Get Mystery Box with random crypto!

#እያገቡ_መፍታት__!! ▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬ ክብር ሆኖ ሳለ ከአሏህ የፀደቀ፡ የነብያት ሱና ሆኖ የታ | Abu_Oubeida~channel

#እያገቡ_መፍታት__!!
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
ክብር ሆኖ ሳለ ከአሏህ የፀደቀ፡
የነብያት ሱና ሆኖ የታወቀ፡
የመጥፎ ነገሮች ግሩም መጠበቂያ፡
ሰው የሚዘራበት ውድ መነቃቂያ፡
ሆኖ ሳለ ትዳር የሰው መታወቂያ፡
ባለንበት ዘመን ሆነ መሳለቂያ፡
ወጣት ከርሱ ሸሸ መስሎት መሳቀቂያ፡
#ምን__ይሻላል_??
ይነበብ ይህ ችግር ተገልፆ መፅሀፉ፡
የሰሙትን ሁሉ አምነው እየፃፉ፡
አሜን ብለው ስንቶች ከእውነት ዘንድ ጠፉ?
መጋባት ፀጋ ነው ብለው ቀርፀውን፡
መረጃን አጣቅሰው ዑስታዞች ነግረውን፡
በአንዳንዶቹ ቀንተን አይተነው ፍሬውን፡
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
ለካ በዚህ ዘመን ትዳር ሆኗል አዳር፡
የጊዜ ቆይታው አፋፍ ነው ወንዝ ዳር፡
ጥቅምት ኒካህ አስረው ያሰርጉታል ህዳር፡
ልምድ ሆኗል አሉ ይሔ ዳር እስከዳር፡
#ወይ__ትዳር__!!
ባልተዋለ ውሎ ባልተቃኘ መንደር፡
ይገመታል እንጂ ያልታየ አይነገር፡
በጣም ያሳዝናል ሴቱም አልታመነ፡
ወንድነቱ ላሽቋል ወንዱም ወንድ አልሆነ፡
የትዳርን ክብር አራካሹ በዝቶ፡
ሀራሙና መጥፎው ዝሙቱ ተስፋፍቶ፡
በስልጣኔ ስም ስሙ ተተክቶ፡
እውነተኛው ትዳር አይቶ ተመልክቶ፡
ዛሬስ ሞተ መሰል ፍቅር ገደል ገብቶ፡
▭▭▭▭▭▭▭▭▭▭▭▭▭
እውነት ፍቅር ሙቷል ለኔ ይመስለኛል፡
በየ ደረስኩበት ከጭቅጭቁ ጋር ፍቹ ይታየኛል፡
ከማይለቅ አሻራ በትካዜ ሟሙተው
በፍቅር መኖርን መግባባትን ትተው፡
እንደ ቀላል ነገር ቀሩ ተለያይተው፡
በፀጉር ስንጠቃ ከተነጋገሩ፡
መፋታት ነው በቃ እንድህ ነው ነገሩ!?
#ኢና_ሊላሒ_ወኢና_ኢለይሒ_ራጂዑን!!
ምን እንኳን ቢከፋ አንድ ይቅርታ በጁ፡
በመቻቻል አምነው ካልሆኑ ዝግጁ፡
በደቡብ በምዕራብ ቢዞሩ በኤጁ፡
ትዳር አይገኝም ምን እድሜ ቢፈጁ፡
ይልቁንስ አግቡ ሳታገቡ አታርጁ፡
#ስለሆነም__
ክብራችን እያለ ተመካክሮ ኑሮ፡
እንድንነጋገር አድርጎ አምላክ ፈጥሮ፡
የምን ልዩነት ነው ምንድን ነው ሚስጥሩ፡
በምን መልክ ልፃፍ አስፈራኝ ነገሩ፡
ሰኞ ተገናኝተው ማክሰኞ መማታት፡
ረቡዕ ተኳርፈው ሀሙስ ላይ መፋታት፡
#ወይ__ሰው__!!
ሰው የፍጥረት ትዕቢት የ'ራስ ፍቅር ፍርፍር፡
የተንኮል ውድ ልጂ ተንሸራታች ስፍር፡
ሰው የእብሪት ነፋስ በእንቅልፉ ሒያጅ እግር፡
በገዛ ፀባዩ የሚኖር በህፀፅ የሚቆይ በችግር፡
ሁሌም ማይገባው፤
የዚህች አለም ቀመር የኑሮ ሽግግር፡
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
#በቃ_እኔ_አላገባም__!!
ሁለት ቀን ለማይቆይ ያገባችሁ ይብላኝ፡
እናንተን እያየሁ ውስጤን እየበላኝ፡
ጥርሴ እየፈገገ መስዬ የደላኝ፡
በናንተ እየመዘንኩ ትዳሩም አስጠላኝ፡
ከሁሉም ልርቅ ነው ከሰው አልግባባም፡
እንደዚህ ከሆነ በቃ እኔ አላገባም፡
#ወላሒ_ሲያስጠላ__!!
ሴቷ ጥሩ መስላ ወንድን ልጅ ማታለል፡
ወንዱ ጀግና መስሎ ሴቶችን ማማለል፡
ሴቱም ሆነ ወንዱ ይዟል መንቀዋለል፡
የሌላትን ውበት ቅባት ተቀባብታ፡
ሁረል አይን መስላ ከልቡ ውስጥ ገብታ፡
በምኑ በምኑ አሳስቃ ገብታ፡
በጨለማ ተገን ሳያስተውል ማታ፡
ቆንጆ ነች ብሎ አምኖ ከጎኑ ተኝታ፡
ለካ ስትታጠብ ጉድ ያላት ገበታ፡
#ውይ_ውይ_ሴት!!
በነጋ በጠባ በፍቅር አስክራው፡
ጠብቀኝ እያለች እንደ ቅርስ አኑራው፡
አስር አይነት ፎቶ ተውባ ልካለት፡
ከልቡ ለመኖር ስጦታ አድርጋለት፡
አዒሻን እንደምቶን ምላ ቃል ገብታለት፡
በስተመጨረሻ ቅባቱ ሲታጠብ፡
ፀባዋ ሲፈተሽ ስትኖር ከቤተሰብ፡
ኢስላምም አስጠላት ተውሒድና ሱና፡
#በቃ_ተለያዩ_ዑሙ_ጀሚል_ሆና፡
#ውይ_ውይ_ወንድ!!
ጀግና ወጣት መስሎ ከባጢል የራቀ፡
ልብስ እየቀየረ በጥርሱ እየሳቀ፡
በሱ ማስመሰያ ስንቱ ሴት አለቀ፡
ኸረ ዑስታዝ ሆኖ ሰው እያስተማረ፡
አዋቂ ነኝ ብሎ ሌላ እየመከረ፡
ከዚህችም ከዚያችም ነገር እየቃመ፡
ይህችንም ያችንም እየጠቋቆመ፡
በቻናሉ መስሎ ለእውነት የቆመ፡
በርሱ የምላስ ቀስት ስንቱ ሴት ታመመ፡
#ውይ___ወንድ__!!
የልጆቹን እናት ከቤቱ ደብቆ፡
ከሚስቱ እየሸሸ በሀራም ተዘፍቆ፡
በሀራም ሰፊና ገብቶ በሸለቆ፡
ገመናው ሲገለፅ ስንቱ ቀረ ወድቆ፡
የሌለውን ነገር ለሴት እየዋሸ፡
ወስነው ሲጠጉት በሩቁ እየሸሸ፡
የስንት እህት ህይወት በርሱ ተበላሸ፡
ወዳጂ ሲጠይቀው ይሆናል ላብ በላብ፡
አብዛኛው ፀባዩ ነው እንደ አቡ ለሀብ፡
#በነዚህ_ምክንያት___!!
የእውነት ጀግኖችን መምረጡ ቸገረን፡
ሁሉም አስጠላና አደነጋገረን፡
እርግጥ ነው ብዙ አሉ እውነተኛ ጀግና፡
ግን የሚስተዋለው ሀራሚው ሆነና፡
ትዳርን ስናስብ እኒህ ትዝ እያሉን፡
እያቀባዘረን ሲዘርፉን ሲበሉን፡
ጥሩወቻችንን ከየት እናምጣቸው፡
ሴት የሚለው ፆታ አንድ አይነት አርጓቸው፡
#በርግጥ_ወንድም_አለ!!
አላማው የሆነ ኢስላምን ማስተማር፡
እጂግ ብርቱ ጀግና ጠንካራ እንደ ሚስማር፡
ተደብቆ እሚኖር ሀላሉ እስክትመጣ፡
ከባለቤቱ ጋር ስኬት የሚጠጣ፡
ግን ይህ አይነቱ ሰው በኔ ተመዝኖ፡
በፆታችን ብቻ ፀባይ ተተምኖ፡
መልካሙ ጠፋ እንጂ መጥፎው ግልፅ ሆኖ፡
#እያገቡ_መፍታት__!!
በእንደዚህ አይነቶች ትዳርን ፈራነው፡
እርሱም እኛን ፈራ በሩቁ ሸሸነው፡
ምንድን ነው ሚሻለን ዝሙቱ ተስፋፋ፡
ወላሒ ጨነቀኝ ሀላል ነገር ጠፋ፡
መፍትሔ እንፈልግ ይህን ጉድ ለመግታት፡
ሰደድ እሳት ሆኗል እያገቡ መፍታት፡
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
በኑረዲን አል አረቢ(#ሰኔ_24_2013)
▬▬▬▬▬▬➋⓪❶❸▬▬▬▬
http://t.me/nuredinal_arebi
http://t.me/nuredinal_arebi
http://t.me/nuredinal_arebi
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬